1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሩሲያ በዩክሪን ላይ አዲስ የአየር ጥቃት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 30 2015

ሩሲያ ነገ የምታከብረዉን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅያ የድል ቀን አስታካ በዩክሬን ከተሞች ላይ በድሮን ጥቃት አደረሰች። ጥቃቱ የተፈፀመዉ በመዲና ኪይቭ እና በሌሎች የዩክሪይን ከተሞች ነዉ። በጥቃቱ እስካሁን ቢያንስ አምስት ሰዎች ጉዳት እንደደ,ሰባቸዉ ተዘግቧል። ጥቃት የጣሉት ድሮኖች ኢራን ሰራሽ ናቸዉ ተብሏል።

https://p.dw.com/p/4R3wA
Ukraine- Krieg I Russischer Beschuss
ምስል Andrew Kravchenko/AP/picture alliance

የሩሲያ የጦር ኃይሎች እስከ ነገ ማክሰኞ የዶንባስ ከተማ ባኽሙትን ለመቆጧጠር እየገሰገሱ ነው ሲሉ የዩክሬን ወታደሮች አስታወቁ። ሩሲያ ባኽሙትን ለመያዝ ተጨማሪ ዘመናዊ መሳሪያዎችን እየዘረጋችና ወታደሮቿን እንደገና እያሰባሰበች መሆኑን፣ የዩክሬን ጦር ቡድን ምሥራቅ አዛዥ ኮሎኔል ኦሌክሳንድር ሲርስኪ የዩክሬንን ጦር ግንባር ከጎበኙ በኋላ ማስታወቃቸዉ ተዘግቧል። የዩክሬኑ ኮሎኔል የሩስያ የጦር ኃይል እስከ ነገ ግንቦት 1 ቀን ድረስ ባኽሙትን ለመቆጣጠር ተስፋ አድርገዋል ባይ ናቸዉ። ዩክሬኑ ፕሬዚደንት ቭላዶሚር ዜሌንስኪ በበኩላቸዉ ይህን የሩስያን ተስፋ ተግባራዊ እንዳይሆን በጥብቅ እንከላከላለን ሲሉ አስረግጠዉ ተናግረዋል። ሩስያ ነገ ማለት የጎርጎረሳዉያኑን ግንቦት 9 ቀን በናዚ ጀርመን ላይ የሶቭየት ሕብረት ጦር ድል የተቀዳጀበት ቀን በመሆኑ «የድል ቀን» የሚል ዕለቱ በሩስያ ልዩ ትርጉም የሚሰጠዉ ነው። ሩስያ ይህን ቀን አስታካ ባኽሙትን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እቅዷን ለማሳካት ኃይሏን አጠናክራ የጦር ድብደባዋን  ተብሏል።  በሌላ በኩል ሩሲያ ወደፊት የሚመጡ መርከቦችን ለመመዝገብ ፈቃደኛ ባለመሆን የጥቁር ባሕር እህል ስምምነትን እንዳቋረጠች ዩክሬይን ገለጸች ። የዩክሬን ጥቁር ባሕር ወደቦች ባለፈው ዓመት ሩሲያ ወረራ ከፈፀመች ወዲህ  ተዘግተው ነበር። ይሁንና  ባለፈው ሐምሌ ወር በሞስኮ በተባበሩት መንግሥታት እና በቱርክ መካከል በተደረሰዉ ስምምነት ዩክሪይን እህል የጫኑ መርከቦችዋን ወደ ሦስቱ ወደቦች  በኩል ስንዴን ጨምሮ የተለያዩ ጥራጥሪዎችን ማሻገር አስችሏት ነበር።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሰ